በከተማ አስተዳደሩ ተግባራዊ የተደረገው የተፋጠነ ትምህርት በሚጠበቀው ደረጃ ውጤታማ እንዲሆን ትምህርት ተቋማት በትኩረት መስራት እንደሚገባቸው ተገለጸ።
(ህዳር 9/2019 ዓ.ም) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የልዩፍላጎትና ጎልማሶች መሰረታዊ ትምህርት ዳይሬክቶሬት የተፋጠነ ትምህርት ተግብረው ውጤታማ ከሆኑ ተቋማት መካከል አንዱ በሆነው ጎሮ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ትምህርቱ ከሚሰጥባቸው ተቋማት የተውጣጡ ርዕሳነ መምህራን እና መምህራን በተገኙበት የልምድ ልውውጥ መርሀግብር አካሂዷል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊና የዘርፉ አስተባባሪ አቶ አሊ ከማል በመርሀግብሩ ባስተላለፉት መልዕክት የተፋጠነ ትምህርት በተለያዩ ምክንያቶች መደበኛ ትምህርታቸውን መከታተል ላልቻሉ ዜጎች በአማራጭነት የሚሰጥ የትምህርት አገልግሎት መሆኑን አስታውሰው የልምድ ልውውጡ ተሳታፊዎች የጎሮ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውጤታማ የሆነበትን አሰራር ተሞክሮ በመውሰድ በየተቋማቸው ተግባራዊ አድርገው ተማሪዎችን ማብቃት እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል።
የለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ሌሊስቱ ተስፋዬ በበኩላቸው በክፍለ ከተማው በ2019 ዓ.ም 726 ተማሪዎች የተፋጠነ ትምህርት በመማር ላይ መሆናቸውን ገልጸው ጎሮ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በክፍለ ከተማው የተፋጠነ ትምህርት ተግባራዊ አድርገው ውጤታማ ከሆኑ ተቋማት መካከል አንዱ መሆኑን አመላክተዋል።
በከተማ አስተዳደሩ የተፋጠነ ትምህርት እድሜያቸው ከ9 እስከ 14 አመት ለሆናቸው ዜጎች ከ1ኛ እስከ 3ኛ ክፍል የሚሰጠው ትምህርት ተጨምቆ በአንድ አመት ፕሮግራም እየተሰጠ መሆኑን የቢሮው የልዩ ፍላጎትና ጎልማሶች መሰረታዊ ትምህርት ዳይሬክተር አቶ ዳንኤል አስራት ጠቁመው ተማሪዎቹ ትምህርቱን ሲያጠናቅቁ በሚሰጣቸው ምዘና መሰረት 50% እና በላይ የሚያስመዘግቡት 4ኛ ክፍል ገብተው መደበኛውን ትምህርት የሚከታተሉበት አማራጭ መመቻቸቱን አስታውቀዋል።
በመርሀ ግብሩ የቢሮው የጎልማሶች መሰረታዊ ትምህርት ባለሙያ አቶ ጌታቸው በላይነህ የተፋጠነ ትምህርት ጽንሰ ሀሳብና አተገባበርን መሰረት ያደረገ ገለጻ ያካሄዱ ሲሆን የጎሮ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር አቶ ይስሀቅ ታምሩ በበኩላቸው ተቋሙ የትምህርት አገልግሎቱን ውጤታማ ያደረገበትን አሰራር ለተሳታፊዎች አቅርበው ውይይት ተካሂዷል።

.