ከትምህርት ገበታ የሚቀዳ ዕውቀት የአንድን ሀገር የነገ ዕጣ ፈንታ እና የታሪክ አቅጣጫ የመወሰን ታላቅ ኃይል አለው።
(መስከረም 18/2019 ዓ.ም) ትምህርት የፊደል መቁጠሪያ መንገድ ብቻ ሳይሆን፣ የሀገርን የወደፊት ዕድል የሚቀርፅ፣ የብልጽግናን ጎዳና የሚያበራ እና በዕውቀት ላይ ተመስርቶ የሀገር ሉዓላዊነትን የሚያስጠብቅ መሣሪያ ነው።
የሀገራችን ሥርዓተ ትምህርት ለብዙ ዓመታት በርካታ መዋቅራዊ ጉድለቶች የነበሩበት ቢሆንም፣ አሁን ላይ ግን ኋላ ቀር አሠራሮችን በመሰናበት፣ ከሀገሪቱ የዕድገት ፍላጎት ጋር የተጣጣመ አዲስ ሥርዓተ ትምህርት መቀረጹ የትውልዱን የነገ ዕድል የሚቀይር ታሪካዊ እርምጃ ሆኗል።
ትምህርት የዕውቀት መቅሰሚያ ብቻ ባለመሆኑ የሀገር ሉዓላዊነትን፣ የቴክኖሎጂ ዕውቀትን፣ እና የኢኮኖሚ ከፍታን የሚያረጋግጡ ጠንካራ ሀገረ መንግሥት ተረካቢ ዜጎች የሚኮተኮቱበት ነው።
የተሻሻለው የትምህርት ሥርዓታችን በተግባር፣ በዲጂታል እና በቴክኖሎጂ አቅም ላይ ያተኮረ በመሆኑ፤ ተማሪዎች የነገውን ዓለም የሚመጥን ብቃት ከወዲሁ እንዲያዳብሩ እያደረጋቸው ይገኛል።
በዚህ የዲጂታል ዘመን በቴክኖሎጂ ፈጠራ ንቅናቄ ላይ የምትገኘው ኢትዮጵያ በየክፍል ደረጃው የምታስተምራቸው ህፃናትና ወጣቶች የበለፀገች ሀገር ለመገንባት በሚደረገው ጥረት ከፊት የሚመሩ ቁልፍ ዜጎች ናቸው።
አዲሱ የትምህርት ዘመን የነገዋን ኢትዮጵያ በዕውቀት፣ በሥነ-ምግባር፣ በሀገር ፍቅር እና በቴክኖሎጂ ፈጠራ ለታነፁ ስልጡን ልጆቿ የማስረከብ የታሪክ ቅብብሎሽ ሂደት አካል ነው።

.