10ኛው ከተማ አቀፍ የተማሪዎችና የመምህራን የሳይንስ የፈጠራ ስራ አውደ ርዕይ በተለያዩ በላድርሻ አካላት በመጎብኘት ላይ ይገኛል፡፡
(ሚያዝያ 17/2017) "በፈጠራ ስራ የተካነ ትጉህ ትውልድ ለሀገር ብልጽግና" በሚል መሪ ቃል ለተከታታይ ሶስት ቀናት እየተካሄደ የሚገኘው ከተማ አቀፍ የሳይንስ አውደ ርዕይ በሁለተኛ ቀን ቆይታው ላይ በተለያዩ በላድርሻ አካላት በመጎብኘት ላይ ይገኛል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ አዘጋጅነት በከተማ አስተዳደሩ በትላንትናው እለት በክብር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተመርቆ ለተመልካች ክፍት የሆነው 10ኛው ከተማ አቀፍ የተማሪዎችና የመምህራን የሳይንስ የፈጠራ ስራ አውደ ርዕይ በዛሬው እለት በተማሪዎች በወላጆችና በትምህርት ባለድርሻ አካላት በመጎብኘት ላይ ይገኛል፡፡
በአውደ ርእዩ በተማሪዎችና በመምህራን የተሰሩ የሳይንስ የሂሳብና ቋንቋ ትምህርት ላይ ትኩረት ያደረጉ እንዲሁም የተለያዩ ችግር ፈቺ የፈጠራ ስራዎች ቀርበዋል፡፡
ጎብኚዎች የፈጠራ ስራው ተማሪዎችና መምህራን ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችሉ ስራዎች ያሳዩበት መሆኑን ጠቁመው የተማሪዎችንና የመምህራንን የፈጠራ ችሎታ ከፍ ወዳለ ደረጃ ለማሳደግ እንዲችሉ የቢሮው እገዛ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡
የሳይንስና ፈጠራ አውደርእዩ የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ ሃላፊዎችና የትምህርት ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በነገው እለት የሚጠናቀቅ ይሆናል፡፡