(ሚያዝያ 24/2017 ዓ.ም) ኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 1 በሚገኘው አቡነ ባሲሊዮስ ትምህርት ቤት በተካሄደው ልምድ ልውውጥ ርዕሳነ መምህራን፣ሱፐር ቫይዘሮች፣ የክፍለ ከተማ የዘርፉ ቡድን መሪዎችና ባለሙያዎችን ጨምሮ ሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው የተለያዩ አካላት የተሳተፉ ሲሆን የልምድ ልውውጡ ተሳታፊዎች የልዩ ፍላጎት ተማሪዎች የሚማሩበትን ክፍል፣የማምረቻ ቦታ እንዲሁም የድጋፍ መስጫ ማዕከሉን ጨምሮ የትምህርት ቤቱን ቅጥር ግቢ ተዘዋውረው ተመልክተዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የልዩፍላጎትና የጎልማሶች መሰረታዊ ትምህርት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ገመቺስ ፍቃዱ ቢሮው ከፍተኛ በጀት መድቦ በየትምህርት ቤቱ ለተቋቋሙ የልዩ ፍላጎት የድጋፍ መስጫ ማዕከላት የተለያዩ ግብአቶችን በማቅረብ ተማሪዎችን ተጠቃሚ በማድረግ ላይ መሆኑን ጠቁመው ይህንን ድጋፍ ተጠቅመው ውጤታማ ከሆኑ ተቋማት መካከል አንዱ አቡነ ባሲሊዮስ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በመሆኑ የልምድ ልውውጥ ፕሮግራሙ መዘጋጀቱን በመግለጽ የመርሀ ግብሩ ተሳታፊዎች በልምድ ልውውጡ ያገኙትን ተሞክሮ መሰረት በማድረግ በየትምህርት ቤቶቻቸው ውጤታማ ስራ መስራት እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል።
የኮልፌ ቀራንዮ ወረዳ 1 ትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሽመልስ ንጉሴ በበኩላቸው አቡነ ባሲሊዮስ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የልዩ ፍላጎት ትምህርትን በአግባቡ ተግባራዊ አድርጎ ውጤታማ መሆን የቻለ ተቋም መሆኑን ለልዩ ፍላጎት ተማሪዎች እና መምህራን ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር የሚሰጡ ስልጠናዎችና በአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ የሚደረጉ የግብአት ድጋፎች በዘርፉ ለታየው ውጤት ያበረከተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን አመላክተዋል።
በመርሀ ግብሩ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የልዩ ፍላጎት ትምህርት ባለሙያ አቶ ፀጋዬ ሁንዴ የልምድ ልውውጡን አላማ እና አስፈላጊነት እንዲሁም የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር አቶ ለገሰ ማሞ በተቋሙ ያለውን የልዩ ፍላጎት ትምህርት አተገባበር የተመለከተ ሰነድ አቅርበው በተሳታፊዎች ውይይት ተካሂዷል።
.