የሁለተኛ መንፈቅ አመት ትምህርት አጀማመርን አስመልክቶ በየትምህርት ቤቱ ክትትል ለሚያደርጉ ባለሙያዎች ኦረንቴሽን ተሰጠ።
(ጥር 30/2017 ዓ.ም) በመርሀ ግብሩ የቢሮው አላማ ፈጻሚ ዳይሬክተሮችና ባለሙያዎችን ጨምሮ የክፍለ ከተማ የስራ አስተባባሪዎችና ባለሙያዎች የተገኙ ሲሆን በከተማ አስተዳደሩ የካቲት 3/2017ዓ.ም የ2ኛ መንፈቅ አመት ትምህርት እንደሚጀመር ቀደም ሲል መገለጹ ይታወቃል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የስርአተ ትምህርት ማበልጸጊያና ትግበራ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው ታለማ ከትምህርት አጀማመሩ ጋር በተገናኘ ክትትል የሚያደርጉ የትምህርት ባለሙያዎችና ሱፐርቫይዘሮች በሁሉም የመንግስትና የግል ትምህርት ቤቶች በመገኘት ቢሮው ባዘጋጀው ቅጽ መሰረት ትክክለኛ መረጃ በመሙላት ግብረ መልስ ማቅረብ እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል።
ዳይሬክተሩ አያይዘውም ምልከታው የትምህርት አጀማመርን አስመልክቶ እንደመካሄዱ በዕለቱ ርዕሳነ መምህራንን ጨምሮ መምህራን እና የአስተዳደር ሰራተኞች መገኘታቸውን በማየት ሪፖርት ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው ጠቁመው በየትምህርት ቤቱ በእለቱ የተማሪዎች ምገባ በሜኑ መሰረት መቅረቡን ማረጋገጥ እንደሚገባቸው አመላክተዋል።
የቢሮው የአጠቃላይ ትምህርት ሱፐርቪዥን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ጥላዬ ዘውዴ በበኩላቸው የ2017ዓ.ም የሁለተኛ መንፈቅ አመት አጀማመርን አስመልክቶ በየትምህርት ቤቱ በሚደረገው ክትትል መምህራን እለታዊ እቅድ በማዘጋጀት በክፍለ ጊዜያቸው መሰረት ማስተማር ስለመጀመራቸው እንዲሁም በሁሉም ተቋማት በቂ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች መሰራታቸውን በማረጋገጥ ለቢሮው ሪፖርት ማድረግ እንደሚገባ ገልጸዋል።
በክትትልና ድጋፉ የሚሳተፉት ባለሙያዎች የተመደቡበት ትምህርት ቤት ከቢሮው የአጠቃላይ ትምህርት ሱፐርቪዥን ቡድን መሪ በሆኑት አቶ ተሾመ ቀናሳ አማካይነት የቀረበ ሲሆን በክትትሉ ለሚሳተፉ ባለሙያዎች ድጋፍ የሚያደርጉ አስተባባሪዎች መመደባቸውም ተገልጿል።
.