(ሚያዝያ 8/2017 ዓ.ም) በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ጽ/ቤት አዘጋጅነት "የፈጠራ ስራን ከቃል ወደ ባህል!" በሚል መሪ ቃል የ2017 ዓ.ም የተማሪዎችና የመምህራን የሳይንስ ፣ ሂሳብ እና የቴክኖሎጂ የፈጠራ ስራዎች አውደ ርዕይና ውድድር በዛሬው ዕለት ተጀምሯል።
በፈጠራ ውድድሩና አውደ ርዕዩ ላይም በክፍለ ከተማው የሚገኙ የመንግስትና የግል 1ኛ እና 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እየተሳተፉ ይገኛሉ።
በመክፈቻ መርሃ ግብሩ ላይም የክፍለ ከተማው ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ መብራቱ ደሴ ጨምሮ ሌሎች የክፍለ ከተማ አመራሮች እና የትምህርት አመራሮች ተገኝተዋል።
የክፍለ ከተማው ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ መብራቱ ደሴ የፈጠራ ስራ ከሃሳብ በመነሳት በተግባር የሚረጋገጥ ጊዜው የሚፈልገው አስገዳጅ ሁኔታ በመሆኑ ተማሪዎችን በመደገፍ የሳይንስና ፈጠራ ስራዎች ክህሎታቸውን ማዳበር እንደሚገባ ጠቁመዋል። አቶ መብራቱ አክለውም የነገ ሀገር ተረካቢ ብቁና ተወዳዳሪ የሳይንስና የፈጠራ ሰዎችን ለማፍራት ትምህርት ቤቶች ላይ በትኩረት መስራት ይገባል ብለዋል።
የክፍለ ከተማው ትምህርት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ በላይ ነጋሽ በበኩላቸው በእያንዳንዱ ሃገራዊ እድገት ውስጥ የፈጠራና የቴክኖሎጂ ስራዎች ትልቁን ድርሻ የሚወስዱ መሆናቸውን ጠቁመው ትምህርት ቤቶችን የቴክኖሎጂና የልህቀት ማእከል ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን መናገራቸዉን ከክፍለ ከተማው ያገኘነው መረጃ ያሳያል።
.