Resource ለክርስትና እምነት ተከታዮች በሙሉ እንኳን ለከተራና ለአየሱስ ክርስቶስ በዓለ ጥምቀት በሰላም አደረሳችሁ!

ለክርስትና እምነት ተከታዮች በሙሉ እንኳን ለከተራና ለአየሱስ ክርስቶስ በዓለ ጥምቀት በሰላም አደረሳችሁ!

18th January, 2025

(ጥር 10/2017 ዓ.ም) ኢየሱስ ክርስቶስ የጠፋውን ሰው አዳምን ለመፈለግ በመጣ ጊዜ እከብር አይል ክቡር የባሕርይ አምላክ ሆኖ ሳለ በዮርዳኖስ ወንዝ በአገልጋዩ (በፍጡሩ) በዮሐንስ ሲጠመቅ እንደሰውነቱ ረግጦ እንደ አምላክነቱ አቅልጦ ያንን የዕዳ ደብዳቤ መደምሰሱን ወደሲኦል ተጥሎ የነበረዉን ደግሞ በእዕለተ ዐርብ በአካለ ነፍስ ወደሲኦል ወርዶ ነፍሳትን ባወጣ ጊዜ ማጥፋቱን እንዲሁም በእርሱ ጥምቀት የእኛን ጥምቀት መቀደሱን ከሀይማኖታዊ አስተምረቶች እንረዳለን፡፡ ከዚህም በሀገራችን በአደባባይ ከሚከበሩ በዓላት መካከል አንዱ ከሆነው የጥምቀት በዓል ከሃይማኖታዊ እሴትነቱ ባሻገር ዝቅ ብሎ ማገልገልንና ለማህበራዊ ትስስራችን መጠናከር ከፍተኛ አስተዋጽዎ ያለው መሆኑን እንማራለን፡፡ 

በአለም መድረክ የኢትዮጵያን ከፍታን ከሚያሳዩና አይን ከሚስቡ በሀገራችን በአደባባይ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቱባ ባህላዊ ትእይንቶቻቸዉን አጎልተዉ ከሚያሳዮባቸዉ እንዲሁም በአልበሳትና በብዝሃ ቋንቋቸዉም ፈክተዉ ከሚታዩባቸው በዓላት መካከል አንዱ የጥምቀት በዓል ሲሆን በአለም በዩኔስኮ ከማይዳሰሱ ቅርሶች መካከልም ተመዝግቦ የሚገኝ ነው፡፡ 

ይህ በዓል ከሃይማኖታዊ በዓልነት ባሻገር የሀገርን መልካም ገጽታን ከመገንባት እና የቱሪስት ፍሰትን ከማጎልበት አንጻር ጉልህ ሚና የሚጫወት በመሆኑ እንግዶችን በፍቅር ተቀብሎ በማስተናገድ በዓሉ በሰላም ተጀምሮ በሰላም እንዲጠናቀቅ ህብረተሰቡ በተለይም ደግሞ የትምህርት ባለድርሻ አካላት ከፀጥታ አካላት ጋር እጅና ጋንት በመሆኑ መስራት ይኖርባችዋል።

በመጨረሻም ለክርስትና እምነት ተከታዮች በሙሉ እንኳን ለከተራና ለአየሱስ ክርስቶስ በዓለ ጥምቀት በሰላም አደረሳችሁ እያልኩ በዓሉ የሰላም ፣ የፍቅር እና የመተሳሰብ በዓል እንዲሆን እመኛለሁ፡፡

አመሰግናለሁ!

ዶ/ር ዘላለም ሙላቱ ደሙ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ሀላፊ


.

Copyright © All rights reserved.