የአቃቂ ክፍለ ከተማ በመንግስትና በግል ትምህርት ቤቶች መካከል ሲያካሂድ የቆየው የተማሪዎችና የመምህራን ስፖርት ሊግ ውድድር ገላን ጉራ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በሚገኘው የስፖርት ማዘውተሪያ ሜዳ በድምቀት ተጠናቀቀ።
(መጋቢት 4/2017 ዓ.ም) በመዝጊያ መርሀ ግብር የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ሳምሶን መለሰን ጨምሮ የክፍለ ከተማው ብልጽግና ፓርቲ ቅርጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዮሀንስ መለሰ፣ የክፍለ ከተማና ወረዳ አመራሮች፣ርዕሳነ መምህራን፣መምህራን ፣ተማሪዎች እንዲሁም ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው የትምህርት ማህበረሰብ አካላት የተገኙ ሲሆን በመምህራን መካከል በእግር ኳስ በተደረገ የዋንጫ ጨዋታ አቃቂ መንግስት ክላስተር ገላን ቁ.2 ክላስተርን 2 ለ 0 በማሸነፍ የዋንጫ ተሸላሚ ሆኗል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ሳምሶን መለሰ በትምህርት ተቋማት የሚካሄዱ ስፖርታዊ ውድድሮች ተማሪዎች በክፍል ውስጥ በንድፈ ሀሳብ የሚማሩትን ትምህርት በተግባር በማሳየት በአካልም ሆነ አዕምሮ የዳበረና ትውልድ ለመፍጠር የሚያስችል ተግባር መሆኑን ገልጸው የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ በተማሪዎችና መምህራን መካከል በዚህ መልኩ ደማቅ ውድድር በማዘጋጀቱ ምስጋና አቅርበው በስፖርታዊ ውድድሩ አሸናፊ ለሆኑ መምህራን እና ተማሪዎች እንኳን ደስ አላችሁ በማለት መልዕክት አስተላልፈዋል።
በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ብልፅግና ፓርቲ ቅ/ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ዮሀንስ ለገሰ ስፖርት የአንድነት መገለጫ ፣ በህዝቦች መካከል ወንድማማችነትንና እህትማማችነትን የሚያጎለብት የዓለም ቋንቋ መሆኑን ጠቅሰው በተማሪዎች መካከል የሚካሄዱ ውድድሮች ተማሪዎች ራሳቸውን በዕውቀት ከመገንባት ባለፈ በአካላል ብቃት ጎልብተው ንቁና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ የሚያስችል በመሆኑ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባና አስተዳዳሩም በተካሄደው የስፖርት ውድድር ላይ ተገቢውን ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን፣ በቀጣይም እነዚህ ድጋፎች ተጠናክረዉ የሚቀጥሉ መሆኑን ገልፀዋል ።
የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ከበደ ድሪባ በበኩላቸው ስፖርታዊ ውድድሩ ለተከታታይ 17 ቀናት በተለያዩ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች በድምቀት ሲካሄድ መቆየቱን ገልጸው በውድድሩ ክፍለ ከተማውን ወክለው በከተማ ደረጃ በሚካሄድ ተመሳሳይ ውድድር የሚሳተፉ ብቁ ስፖርተኞች መመልመላቸውን አስታውቀዋል።
በስፖርታዊ ውድድሩ የመዝጊያ መርሀግብር በአትሌቲክስ፣ጠረጴዛ ቴኒስ፣ቼዝ፣ቅርጫት ኳስ፣መረብ ኳስ ፣በእግር ኳስ እንዲሁም በሽብርቅ አሸናፊ የሆኑ መምህራን እና ተማሪዎች ከክብር እንግዶች የዋንጫ እና ሜዳልያ ሽልማት የተበረከተ ሲሆን ውድድሩ በ ኬት እንዲካሄድ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላትም የምስጋና ምስክር ወረቀት ተሰቷል።
.