የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የዘርፈ ብዙና ቀዳማይ ልጅነት ትግበራ ዳይሬክቶሬት በዘርፈ ብዙ ጉዳዮች ቡድን አዘጋጅነት በዓለም አቀፍ ለ114 ኛ በሀገራችን ለ 49ኛ ጊዜ የሚከበረውን ማርች 8 የሴቶች ቀንን "ፈጣንና ቀጣይነት ያለው ሁሉን አቀፍ ለውጥ በሴቶች ተሳትፎ ይረጋገጣል " በሚል መሪ ቃል የቢሮው አጠቃላይ ሰራተኞች በተገኙበት አክብራል::
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዘላለም ሙላቱ በአሉ ሲከበር ተገኝተው ባስተላለፉት መልእክት ቀደም ሲል በኢትዮጵያ ታሪክ ፖለቲካዊ ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተሳትፎ ትልቅ ተፅዕኖ የፈጠሩ ሴቶች እንደነበሩ አውስተው ኢትዮጵያ በስልጣኔ ፈርቀዳጅ በሆነችበት ስርዓት ውስጥ የሴቶች ሚና ትልቅ እንደነበር ተናግረዋል::
ዶክተር ዘላለም አያይዘው በአሁን ወቅት ሴቶች በመሪነት በሚያስተዳድሯቸው ተቋማት ትልቅ ውጤት እያመጡ መሆኑን ገልፀው ቢሮውም ቀኑን ከማክበር ባለፈ የትምህርት ተደራሽነት በማስፋት በትምህርት ሴክተሩ የፆታ ምጥጥንን በመደገፍና በማብቃት ረገድ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ተናግረው የበዓሉ ተሳታፊ ወንዶች ለሴቶች አጋር መሆን ሴቶችም ራሳቸውን ለማሳደግና ሌሎች ሴቶችን ለመደገፍ መዘጋጀት አለባችሁ ብለዋል::
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ወንድሙ ዑመር በበኩላቸው የሴቶች ቀንን ስናከብር ሴቶች በዓለም አቀፍና በሐገራችን ያጋጠሟቸውን ችግሮች ለመፍታት ያደረጉትን ትግል ልናስታውስ ይገባል ብለዋል::
አቶ ወንድሙ አያይዘውም በአሉን ስናከብር ሴቶች ከቤት ውጪ ባላቸው ተሳትፎ ማህበራዊ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተሳትፏቸውን እንዲያሳድጉና ከወንዶች እኩል አስተዋፅኦ እንዲያደርጉ ቅስቀሳ የምናደርግበት መሆን አለበት ብለው ለትግበራው መሳካት ደግሞ የትምህርት ተቋማት ድርሻቸው ከፍተኛ እንደሆነ ተናግረዋል ::
የቢሮው የዘርፈ ብዙ ጉዳዮች ትግበራ ቡድን መሪ አቶ ይልማ ተሾመ ቀኑን አስመልክቶ የመወያያ ሰነድ አቅርበዋል::
የብሄራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተ መፃህፍትና አገልግሎት የሴቶችና ሕፃናት ክፍል ዳይሬክተር የሆኑት ወ /ሮ ሀገሬ መኮንን የሕይወት ልምዳቸውን አካፍለዋል ፤ በተጨማሪም ለቢሮው የልዩ ፍላጎት አጋዥ የሆኑ መፃህፍትን በስጦታ አበርክተዋል::
የእንጦጦ አምባ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የስርዓተ ፆታ ክበብ አባላት ቀኑን የተመለከተ ሙዚቃና ስነፅሁፋዊ ሥራዎች አቅርበዋል::
.