About በአዲስ ኢንተርናሽናል ኮንቬንሽን ማዕከል ግንቦት 23 እና 24 የትምህርት ቤቶች ፌስቲቫል (school Festival) እንደሚካሄድ ተገለጸ።

በአዲስ ኢንተርናሽናል ኮንቬንሽን ማዕከል ግንቦት 23 እና 24 የትምህርት ቤቶች ፌስቲቫል (school Festival) እንደሚካሄድ ተገለጸ።

17th April, 2025

(ሚያዝያ 8/2017 ዓ.ም) ቬስቲቫሉ ትምህርት ቤቶች ራሳቸውን እንዲያስተዋውቁ እና እርስ በእርስ ልምድ እንዲለዋወጡ የሚያስችል መርሀግብር መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ  ፌስቲቫሉን በአጋርነት ከሚያዘጋጀው ቅሩንፉድ  ዲጂታልስ ከተሰኘው ድርጅት ጋር በጋራ በመሆን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ተገልጿል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ዲናኦል ጫላ በፌስቲቫሉ በከተማ አስተዳደሩ ከሚገኙ 1,500 በላይ ትምህርት ቤቶች መካከል የተመረጡ 500 ተቋማት እንደሚሳተፉ ጠቁመው መርሀግብሩ ትምህርት ቤቶች ራሳቸውን ለህብረተሰቡ በአግባቡ የሚያስተዋውቁበት እና ልምድ የሚለዋወጡበት እንደመሆኑ ቢሮው የቅርብ ክትትል የሚያደርግ መሆኑን አመላክተዋል። 

በፌስቲቫሉ የመንግስት ከግል እንዲሁም አለም አቀፍ ትምህርት ቤቶች  እንደሚሳተፉ  የቅሩንፉድ ዲጂታልስ ስራ አስካሄጅ አቶ መቅድም ደረጀ ጠቁመው በፌስቲቫሉ ከትምህርት ቤቶች ባሻገር በትምህርት ዘርፉ የተለያዩ ተግባራትን የሚያከናውኑ ተቋማት የሚሳተፉ መሆኑን በመግለጽ በመርሀ ግብሩ ታላቁ አትሌት ሻለቃ ሀይሌ ገብረስላሴን ጨምሮ የተለያዩ ተጽኖ ፈጣሪ ኢትዮጵያውያን ተማሪዎችን የሚያበረታቱበት ፕሮግራም መዘጋጀቱን አስታውቀዋል።

በተያያዘ የትምህርት ፌስቲቫሉ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ እና በትምህርትና ስልጠና ቁጥጥር ባለስልጣን ዕውቅና የሚካሄድ  መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ወንድሙ ኡመር መርሀግብሩን አስመልክቶ ከግል ትምህርት ቤት ባለቤቶች ጋር በተካሄደ ውይይት ገልጸው ፌስቲቫሉ ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ እንደመካሄዱ ትምህርት ቤቶች ራሳቸውን ለህብረተሰቡ በአግባቡ የማስተዋወቅ አጋጣሚውን መጠቀም እንደሚገባቸው አስገንዝዋል።

ተማሪዎች ፌስቲቫሉን ያለምንም ክፍያ በነጻ የሚታደሙ  መሆኑን እና ወላጆች ለመግቢያ የሚከፍሉት 100 ብር ለሜቄዶንያ የአረጋውያን እና አእምሮ ህሙማን መርጃ በጎ አድራጎት ድርጅት ገቢ እንደሚደረግ በጋዜጣዊ መግለጫው ተገልጿል።

.

Copyright © All rights reserved.