Home ከጥር 23/2018 ዓ.ም ጀምሮ ሲካሄድ የቆየው 2ኛው ከተማ አቀፍ የተማሪዎች የስፖርት ሊግ እና የመምህራን ስፖርታዊ ውድድር ተጠናቀቀ።

ከጥር 23/2018 ዓ.ም ጀምሮ ሲካሄድ የቆየው 2ኛው ከተማ አቀፍ የተማሪዎች የስፖርት ሊግ እና የመምህራን ስፖርታዊ ውድድር ተጠናቀቀ።

21st February, 2026

በአዲስ አበባ ስቴዲየም በድምቀት በተካሄደው የመዝጊያ መርሀግብር በየደረጃው የሚገኙ የትምህርት እና የስፖርት አመራሮችን ጨምሮ መምህራን፣ወላጆች፣ተማሪዎች እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው የክብር እንግዶች የተገኙ ሲሆን በመርሀግብሩ ከሁሉም ክፍለ ከተሞች በተውጣጡ መምህራንና ተማሪዎች የተለያዩ ትርኢቶች ለታዳሚው ቀርበዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ እና የመዝጊያ መርሀግብሩ የክብር እንግዳ ክቡር ዶክተር ዘላለም ሙላቱ ባስተላለፉት መልዕክት በተማሪዎችና መምህራን መካከል የሚካሄድ ስፖርታዊ ውድድር ጤናማ እና ብቁ አዕምሮ  በመገንባት ለሀገር ብልጽግና መረጋገጥ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ከመሆኑ ባሻገር ተማሪዎችና መምህራን የእርስ በእርስ ግንኙነታቸው እንዲጠናከር የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ በመሆኑ ቢሮው ውድድሩ ተጠናክሮ እንዲቀጥል በትኩረት የሚሰራ መሆኑን አስገንዝበዋል።

ኃላፊው አያይዘውም 2ኛው ከተማ አቀፍ የተማሪዎች የስፖርት ሊግ እና የመምህራን ስፖርታዊ ውድድር ከትምህርት ቤት ጀምሮ በወረዳና ክፍለ ከተማ ደረጃ ሲካሄድ ቆይቶ አሸናፊ በመሆን የተመረጡ ተወዳዳሪዎች በከተማ አቀፉ ውድድር እንዲሳተፉ መደረጉን ገልጸው የዘንድሮው ውድድር ደረጃቸውን የጠበቁ በርካታ የስፖርት ማዘውተሪያ ሜዳዎች ዝግጁ በተደረጉበት አመት መካሄዱ ለየት እንደሚያደርገው ጠቁመው ውድድሩ በስኬት እንዲጠናቀቅ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ለተወጡ ተወዳዳሪ መምህራንና ተማሪዎች እንዲሁም ለሁሉም ለባለድርሻ አካላት ምስጋና አቅርበዋል። 

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ዳዊት ትርፉ በበኩላቸው በተማሪዎችና መምህራን መካከል የሚካሄድ ውድድር ተተኪ ስፖርተኞችን በማፍራት አሸናፊ ብሔራዊ ቡድን ለመገንባት የተጀመረው እንቅስቃሴ ውጤታማ እንዲሆን ከማስቻሉ ባሻገር ተማሪዎች በክፍል ውስጥ በንድፈ ሀሳብ የተማሩትን ትምህርት ተግባራዊ እንዲያደርጉ እድል የሚሰጥ መሆኑን ገልጸው ውድድሩ ስኬታማ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ እና ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ በቅንጅት  መስራታቸውን  አስታውቀዋል።

የአዲስ አበባ መምህራን ማህበር ፕሬዘዳንት አቶ ድንቃለም ቶሎሳ የዘንድሮው ውድድር 6,191 መምህራን በማህበር ተደራጅተው የመኖሪያ ቤት ግንባታ በጀመሩበት ወቅት መካሄዱ ለየት እንደሚያደርገው ጠቁመው ስፖርታዊ ውድድሩ ስኬታማ ሆኖ እንዲጠናቀቅ  መምህራን ላሳዩት ዲሲፒሊን ምስጋና አቅርበዋል።

ስፖርታዊ ውድድሩ ከጥር 23/2018 ዓ.ም ጀምሮ ከ5ኛ እስከ 8ኛ ክፍል የሚማሩ ተማሪዎች በ7 የስፖርት አይነቶች ፣ ከ9ኛ እስከ 12ኛ የሚማሩ ተማሪዎች በ10 የስፖርት አይነቶች እንዲሁም መምህራን በ7 የስፖርት አይነቶች ውድድራቸውን አካሂደው ላሸነፉ  ተወዳዳሪዎች የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዘዳንትና የኦሎምፒክ ጀግናው ኮማንደር ስለሺ ስህን እንዲሁም ሌሎች የክብር እንግዶች የዋንጫ፣የሜዳልያና የሰርተፊኬት ሽልማት ተበርክቷል።


.

Copyright © All rights reserved.