"በአካሉ ብቁና በአዕምሮው ንቁ ትውልድ ለሀገር ብልጽግና"በሚል መሪ ቃል ሲካሄድ በቆየው ክፍለ ከተማ አቀፍ ውድድር በክፍለከተማው ከሚገኙ ትምህርት ቤቶች የተውጣጡ ተማሪዎች እና መምህራን በተለያዩ የስፖርት አይነቶች ተወዳድረው አሸናፊ ለሆኑት በክብር እንግዶች የዋንጫ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ እና የመዝጊያ መርሀግብሩ የክብር እንግዳ አቶ ተስፋዬ አበራ በትምህርት ቤቶች የሚካሄድ ስፖርታዊ ውድድር ተማሪዎች በአካል ብቃታቸው ዳብረው በትምህርታቸው ውጤታማ እንዲሆኑ ከማስቻሉ ባሻገር በተወዳዳሪ ተማሪዎችና መምህራን መካከል ወዳጅነትን የሚያጠናክር መርሀግብር መሆኑን ገልጸው የየካ ክፍለ ከተማ ትምህርት ጽህፈት ቤት ውድድሩ በስኬት እንዲጠናቀቅ ባለድርሻ አካላትን በማስተባበር ላከናወነው ተግባር ምስጋና አቅርበዋል።
የየካ ክፍለ ከተማ ትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፈይሳ ወዳጆ በበኩላቸው የተማሪዎች የስፖርት ሊግ እና የመምህራን ውድድር ሁለንተናዊ ስብዕናው የተገነባ ትውልድ ከመፍጠር ባሻገር ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት የሚያስችል መርሀግብር መሆኑን ጠቁመው ትምህርት ቤቶች የታዳጊ ስፖርተኞች መገኛ እንደመሆናቸው በክፍለ ከተማ ደረጃ የተካሄደው ውድድር ተተኪ ስፖርተኞች የተገኙበት መሆኑን በመግለጽ በክፍለ ከተማ ደረጃ በተካሄደው ውድድር አሸናፊ በመሆን የተመረጡ ተወዳዳሪዎች በቀጣይ በከተማ ደረጃ በሚካሄድ ተመሳሳይ መርሀግብር ክፍለ ከተማውን ወክለው የሚሳተፉ መሆኑን አስገንዝበዋል።
የክፍለ ከተማው ወጣቶችና ስፖርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ መስከረም በቀለ ውድድሩ በድምቀት ከመካሄዱ ባሻገር ክፍለ ከተማውን የሚወክሉ ብቁ ስፖርተኞች የተገኙበት መርሀግብር እንደነበረ አስታውቀዋል።
በውድድሩ ማጠቃለያ በወረዳ አንድ እና ወረዳ ስድስት መምህራን መካከል የእግር ኳስ የፍጻሜ ጫወታ ተካሂዶ ወረዳ አንድ 2 ለ 1 አሸንፎ የዋንጫ ባለቤት ሆኗል።
.