የ2018 ዓ.ም የትምህርት አመት የሞዴል ፈተና ውጤታማ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ክፍለከተሞች ተገቢውን የቅድመ ዝግጅት ስራ መስራት እንደሚገባቸው ተገለጸ።
(ሚያዝያ 30/2018 ዓ.ም) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የፈተና ዝግጅትና አስተዳደር ዳይሬክቶሬት በ2018 ዓ.ም የትምህርት ዘመን ለ6ኛ ፣8ኛ እና 12ኛ ክፍል ተማሪዎች የሚሰጠው ሞዴል ፈተና ስኬታማ እንዲሆን መከናወን በሚገባቸው የቅድመ ዝግጅት ተግባራት ዙሪያ ከክፍለ ከተማ ትምህርት ጽህፈት ቤት የዘርፉ የስራ አስተባባሪዎች ጋር ውይይት አካሄደ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊና የዘርፉ አስተባባሪ አቶ ተስፋዬ አበራ የ6ኛ ፣ 8ኛ እና 12ኛ ክፍል ተማሪዎች የሚወስዱት የሞዴል ፈተና ተማሪዎቹ ያሉበትን ደረጃ አውቀው ለዋናው ፈተና በአግባቡ ዝግጁ እንዲሆኑ የሚያስችል መሆኑን ገልጸው ተማሪዎቹን የሚያስፈትኑ ትምህርት ቤቶች ከወዲሁ በቂ የቅድመ ዝግጅት ስራ መስራት እንዲችሉ ክፍለ ከተሞች አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል ማድረግ እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል።
ምክትል ቢሮ ኃላፊው አያይዘውም ከሞዴል ፈተናው ባሻገር ዋናው የክልል አቀፍም ሆነ ሀገር አቀፉ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ክፍለ ከተሞች ፈተናውን የሚያስተባብሩ የቴክኒክ ኮሚቴዎችን እና በዋና ስራ አስፈጻሚ የሚመራ ኮማንድ ፖስት ማደራጀት እንደሚገባቸው አመላክተዋል
.