የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ በ2018 የትምህርት ዘመን ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ ያከናወናቸው ተግባራት የመማር ማስተማር ስራው ውጤታማ እንዲሆን ያበረከተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑ ተገለጸ።
(ነሀሴ 26/2018 ዓ.ም) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ 33ኛውን ከተማ አቀፍ የትምህርት ጉባኤ ብሩህ ነገን በዛሬ አዕምሮዎች! በሚል መሪ ሀሳብ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በአድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም በሚገኘው ፓን አፍሪክ አዳራሽ አካሄደ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ እና የትምህርት ጉባኤው የክብር እንግዳ ክብርት ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በመርሀግብሩ መክፈቻ ባስተላለፉት መልዕክት ጉባኤው የትምህርት ጥራትን እና ተደራሽነትን ለማረጋገጥ የተከናወኑ ተግባራትን በመገምገም ጠንካራ ስራዎችን አጠናክሮ ለማስቀጠል እና በሂደት የታዩ ጉድለቶችን በማረም የመማር ማስተማር ስራው ውጤታማ እንዲሆን ቀጣይ አቅጣጫ የሚቀመጥበት መርሀግብር መሆኑን ጠቁመው በከተማ አስተዳደሩ በ2018 የትምህርት ዘመን በ6ኛ እና 8ኛ ክፍል የተመዘገበው አበረታች ውጤት በ12ኛ ክፍል እንዲደገም ሁሉም ባለድርሻ አካል ትኩረት አድርጎ መስራት እንደሚገባው አስገንዝበዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ክቡር ዶክተር ዘላለም ሙላቱ በበኩላቸው በከተማ አስተዳደሩ በ2018 የትምህርት ዘመን የትምህርት ፍትሀዊነትን ለማረጋገጥ በርካታ አዳዲስ ተቋማት ተገንብተው አገልግሎት እንዲሰጡ ከመደረጉ ባሻገር የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻል በተሰሩ ስራዎች 23 የመንግስት ትምህርት ቤቶች ደረጃ አራት ላይ መድረሳቸውን አመላክተዋል።
ኃላፊው አያይዘውም በበጀት አመቱ በትምህርት ልማት ስራው ለተመዘገበው ውጤት ከተማ አስተዳደሩ ያደረገው ድጋፍ እና የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ የነበራቸው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን አስታውሰው በጉባኤው የሚቀመጡ የትኩረት አቅጣጫዎችን መሰረት በማድረግ በ2019 የትምህርት ዘመን የተማሪዎች ውጤትና ስነምግባር እንዲሻሻል እንዲሁም በትምህርት ተቋማት ሰላማዊ የመማር ማስተማር ስርአት እንዲጎለብት ቢሮው ትኩረት አድርጎ የሚሰራ መሆኑን አመላክተዋል።
በጉባኤው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ሳምሶን መለሰ የ2018 የትምህርት ዘመን እቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ፤ የቢሮ ሪፎርም ዳይሬክተር አቶ ፋንታሁን እያዩ የተቋማት ምዘና አፈጻጸም ሪፖርት ከማቅረባቸው ባሻገር የአዲስ አበባ መምህራን ማህበር ፕሬዘዳንት አቶ ድንቃለም ቶሎሳ እና የኢትዮጵያና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተማሪ ወላጅ ማህበር ፕሬዝዳንት አቶ ሀሰን ሽፋ መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን በበጀት አመቱ የተሻለ አፈጻጸም ላስመዘገቡ ተቋማት እና የላቀ ውጤት ላመጡ ተማሪዎች ዕውቅና ተሰጥቷል።


.