አፋር ክልል ከሚገኘው አፋር ታለንት አካዳሚ አዳሪ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የመጡ ተማሪዎች በከተማ አስተዳደሩ የሚገኙ አዳሪ ትምህርት ቤቶችን ጎበኙ።
(የካቲት 6/2017 ዓ.ም) ተማሪዎቹ የአድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየምን ጨምሮ የእቴጌ መነን የልጃገረዶች እና የገላን የወንዶች አዳሪ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤትን እንዲሁም ብርሀን የአይነስውራን አዳሪ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን ተዘዋውረው ተመልክተዋል።
በጉብኝቱ የተሳተፉት ተማሪዎች የአፋር ክልል ትምህርት ቢሮ ከሰመራ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ያዘጋጀውን ፈተና በማለፍ በአፋር ታለንት አካዳሚ አዳሪ ትምህርት ቤት ከ9ኛ እስከ 12ኛ ክፍል በመማር ላይ የሚገኙ ተማሪዎች መሆናቸውን የአካዳሚው የቴክኒክ ኮሚቴ አባል አቶ መሀመድ ሰኢድ ጠቁመው ጉብኝቱ ተማሪዎቹ የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ መዲና በሆነችው አዲስ አበባ ከተማ የአንደኛ ሴሚስቴር ትምህርታቸውን ባጠናቀቁበት ወቅት ያደረጉት ጉብኝት በቀጣይ የትምህርት ጊዜያቸው ውጤታማ መሆን እንዲችሉ ተነሳሽነትን እንደሚፈጥርላቸው አስረድተዋል።
አቶ መሀመድ አያይዘውም የአፋር ታለንት አካዳሚ ከተቋቋመ ቅርብ ጊዜ እንደመሆኑ አዲስ አበባ ባሉት አዳሪ ትምህርት ቤቶቹ ያለው አደረጃጀትን ጨምሮ የአስተዳደር ስራዎችና አጠቃላይ የመማር ማስተማር ስራ ልምድ የቀሰሙበት መሆኑን ገልጸው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ከአቀባበል ጀምሮ ተቋማቱን እንዲጎበኙ እድል በማመቻቸት ላደረገው ድጋፍ እንዲሁም የአዳሪ ትምህርት ቤቶቹ አመራሮችና ሰራተኞች ላደረጉላቸው አቀባበል ምስጋና አቅርበዋል።
የጉብኝቱ ተሳታፊዎች ለአዳሪ ትምህርት ቤቶቹ የአፋር ክልል የቱሪዝም መስህብ የሆኑት የሉሲ እና ኤርታሌን ጨምሮ ሌሎች የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎችን ምስል በስጦታ መልክ አቅርበዋል።