የመማሪያ ክፍሎቹ ኢትዮጵያን ሴንተር ፎር ዲቭሎፕመንት (ECD) የተሰኘ ግብረ ሰናይ ድርጅት የትምህርት ቤቱን ማህበረሰብና የተማሪ ወላጆችን በማስተባበር አስገንብቶ ለአገልግሎት ማብቃቱን በምረቃ መርሀግብሩ ተገልጿል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ጥላዬ ዘውዴ ከተማ አስተዳደሩ ለቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት በሰጠው ከፍተኛ ትኩረት በርካታ አዳዲስ ትምህርት ቤቶች ተገንብተው አገልግሎት እንዲሰጡ ከመደረጉ ባሻገር ተቋማቱ ጫወታን መሰረት ያደረገ የማስተማርያ ስነ ዘዴን በአግባቡ ተግባራዊ ማድረግ እንዲችሉ ለመምህራን የአቅም ግንባታ ስልጠና የመስጠትና በከፍተኛ በጀት የግብአት ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን አስታውሰው በአሁኑ ወቅት በርካታ ተቋማት የተደረገላቸውን ድጋፍ በአግባቡ ተጠቅመው ሞዴል በመሆን ለሌሎች ተቋማት ልምድ በማካፈል ላይ እንደሚገኙ አስታውቀዋል።
ምክትል ቢሮ ኃላፊው አያይዘውም ኢትዮጵያን ሴንተር ፎር ዲቭሎፕመንት የአከባቢውን ማህበረሰብ በማስተባበር አቡነ ባስሊዮስ ቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት 3 የመማሪያ ክፍል በመገንባት ለአገልግሎት በማብቃቱ ምስጋና አቅርበው የትምህርት ቤቱ ማህበረሰብም የመማሪያ ክፍሎቹን በአግባቡ ተጠቅሞ ተማሪዎቹን ውጤታማ ማድረግ እንደሚገባው አገንዝበዋል።
የኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ገነነ ዘውዴ በበኩላቸው በአቡነ ባስሊዮስ ቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተገንብቶ አገልግሎት መስጠት የጀመረው የመማሪያ ክፍል ትምህርት ቤቱን ከፈረቃ ትምህርት ከማውጣቱ ባሻገር ከህብረተሰቡ ለረጅም ጊዜ ሲነሳ የነበረ ጥያቄ ምላሽ የሰጠ መሆኑን ጠቁመው ግንባታው ስኬታማ እንዲሆን ድጋፍ ላደረገው የኢትዮጵያን ሴንተር ፎር ዲቭሎፕመንት እንዲሁም ለትምህርት ቤቱ ማህበረሰብና ወላጆች ምስጋና አቅርበዋል።
የኢትዮጵያን ሴንተር ፎር ዲቭሎፕመንት (ECD) ዋና ስራአስካሄጅ ወይዘሮ ሀረገወይን አሸናፊ ድርጅታቸው በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በ16 ቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ ገልጸው ድርጅታቸው በአቡነ ባስሊዮስ ቅድመ አንደኛ ትምህርት ቤት የአከባቢውን ነዋሪ በማስተባበር ከመማሪያ ክፍሎቹ ባሻገር መጸዳጃ ቤት ገንብቶ ለአገልግሎት ማብቃቱን ገልጸው የትምህርት ቤቱ አመራሮች ወላጆችን በማስተባበር ለፕሮጀክቱ ግንባታ ላበረከቱት አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርበዋል።
.