ቢሮው ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በጋራ በመሆን ለ1ኛና 2ኛ ደረጃ አጠቃላይ ትምህርት ሱፐርቫይዘሮች የአቅም ግንባታ ስልጠና መስጠት ጀመረ።
(የካቲት 21/2017 ዓ.ም) ስልጠናው አምስት ርዕሰ ጉዳዮችን መሰረት አድርጎ ለተከታታይ ሶስት ቀናት በዩኒቨርሲቲው የዘርፉ ምሁራን የሚሰጥ መሆኑን በስልጠናው የመክፈቻ መርሀግብር ተገልጿል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዘላለም ሙላቱ በስልጠናው የመክፈቻ መርሀግብር ባስተላለፉት መልዕክት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በማህበረሰብ አገልግሎት የሚያከናውናቸው ተግባራት አካል በማድረግ በከተማ አስተዳደሩ ለሚገኙ የአጠቃላይ ትምህርት ሱፐርቫይዘሮች በዚህ ደረጃ ተዘጋጅቶ ሙያዊ ክህሎታቸውን የሚያሳድጉበትን ስልጠና በመስጠቱ ከፍተኛ ምስጋና አቅርበው የስልጠናው ተሳታፊ ሱፐርቫይዘሮችም በስራ ወቅት የሚስተዋሉ የአሰራርም ሆነ ሙያዊ ህጸጾችን መነሻ በማድረግ ስልጠናውን ከሚሰጡ ምሁራን ጋር በመወያየት ለመማር ማስተማር ስራው ውጤታማነት የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት በአግባቡ ሊወጡ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዘዳንት ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ጋር በጋራ በመሆን የተለያዩ ተግባራትን በማከናወን ላይ መሆኑን በመግለጽ በዩኒቨርሲቲው ምሁራን ለሱፐርቫይዘሮች የሚሰጠው ሙያዊ ስልጠና በትምህርት ጥራትን ለማሳደግ የሚኖረው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን አመላክተዋል።
የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመሆን ለሱፐርቫይዘሮች የሚሰጠው ሙያዊ ስልጠና በዘርፉ ከፍተኛ ልምድ ባላቸው ምሁራን የሚሰጥ እንደመሆኑ ሱፐርቫይዘሮች እስከ ክፍል ድረስ የሚያደርጉት የሱፐርቪዥን ስራ ውጤታማ ሆኖ የመማር ማስተማር ስራውን ስኬታማ እንደሚያደርግ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ አሊ ከማል አስታውቀዋል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የትምህርትና ቋንቋዎች ጥናት ኮሌጅ ተጠባባቂ ኤክስኪዩቲቪ ዲን የሆኑት ዶ/ር የቆየአለም ደሴ የስልጠናዉን ቆይታ አስመልከተው በመድረኩ ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡